by Dawit Atreso
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለማችንን ትልቁን የጤና ተቋም የዓለም የጤና ድርጅትን ለሁለተኛ ዙር እንዲመሩ ዳግም ተመረጡ።የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ብቸኛ ዕጩ ሆነው ዳግም መመረጣቸው የተረጋገጠው በጄኔቫ ላይ እየተካሄደ በሚገኘው 75ኛው የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላላ ጉብዔ ላይ ነው።
ዶክተር ቴድሮስ ያለተፎካካሪ በብቸኛ ዕጩነት በቀረቡበት መድረክ ላይ ከተለያዩ የድርጅቱ አባል አገራት ለዕጩነት ለተሰጣቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ተቋሙን በይፋ ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለሁለተኛ ዙር መምራት ይጀምራሉ መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል::
Doctor Tewodros Adehanom 24/05/2022
" በወረርሽኝ፣ በድርቅ፣ በረሃብ እና በጦርነት ምክንያት አስፈሪ ሁኔታን ተጋፍጠናል " - ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
ዓለም የኮቪድ 19-ወረርሽኝ ወረርሽኝን፣ የዩክሬን ጦርነትን እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ሞንኪፖክስ)ን ጨምሮ አስፈሪ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ይህንን ያሉት የተባበሩት መንግሥታት የጤና ባለሥልጣናት ከአፍሪካ ውጪ በ15 አገራት በተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ዙሪያ በጀኔቫ በተካሄደው ውይይት ላይ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው እስካሁን በመላው ዓለም 92 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ 28 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳይያዙ እንዳልቀረ ተጠርጥሯል።
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ፤ " በዓለማችን ያለው ቀውስ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ብቻ አይደለም። በዓለም ዙሪያ ያሉ ባልደረቦቻችን በዲሞክራቲክ ኮንጎ ለኢቦላ ወረርሽኝ ፣ በአፍጋኒስታን ፣ በኢትዮጵያ ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶሪያ፣ በዩክሬንና በየመን ደግሞ ውስብስብ ለሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት እየሰሩ ነው" ብለዋል።
" በወረርሽኝ፣ በድርቅ፣ በረሃብ እና በጦርነት ምክንያት አስፈሪ ሁኔታን ተጋፍጠናል " ሲሉ መግለፃቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።